Image placeholder
ወንድማማችነት እና እህትማማችነት እንዲጎለብት ሚዲያ የማይተካ ሚና አለው! #አቶ አለማየሁ እጅጉ
By web admin | 2023-10-28

በብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ማስተባበሪያ ዘርፍ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች የ2016 ዓ/ም በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት አፈፃፀምን በመገምገም የቀጣይ አቅጣጫዎችን የጋራ አድርገዋል።

በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ አቅጣጫ የሰጡት የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅ/ጽ/ቤት ም/ሀላፊ እና የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ አቶ አለማየሁ እጅጉ የሚዲያ እና የህዝብ ግንኙነት ስራ ለተቋማችንም ለከተማችንም የጀርባ አጥንት በመሆኑ ሚናውን በአግባቡ እንዲወጣ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ወንድማማችነት እና እህትማማችነት እንዲጎለብትና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር ሚዲያ የማይተካ ሚና አለው ያሉት አቶ አለማየሁ ዘርፉን ሁሉም አመራር በደጋፊነት ሳይሆን በባለቤትነት እንደሚመራው አስረድተዋል።

የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅ/ጽ/ቤት ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ማስተባበሪያ ዘርፍ ሀላፊ ዶ/ር ሚኤሳ ኤለማ በውይይቱ ላይ እንደገለፁት ዘርፉ የፓርቲው ፕሮግራሞች፣ እሳቤዎች፣ ፖሊሲዎች፣ ማኒፌስቶዎችና ዕቅዶች በአግባቡ ተተግብረው የህዝባችንን ኑሮ እንዲያሻሽሉ የበኩሉን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ከአባቶቻችን ወረቶች ላይ የራሳችንን አሻራ በማሳረፍ በታሪክ አጋጣሚ የተፈጠረውን የትውልድ ክፍተት መሙላት ይገባል ያሉት ዶ/ር ሚኤሳ ለዚህም የጋራ ድሎች፣ የጋራ ታሪኮች ያሉን ህዝብ ስለሆነን የወል ማንነትን መገንባት ይገባል ብለዋል።

ከአገር አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተመሰከረላቸው የሚገኙ አንፀባራቂ ሰው ተኮር ተግባራት የበለጠ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እስከ ታች ያሉ የዘርፉን መዋቅሮች አቅም በማጎልበት እንዲሁም በቴክኖሎጂ በመደገፍ የህዝባችንና የከተማ አስተዳደራችንን የተቀናጀ ጥረት ለማጠናከር በቀጣይም ተገቢው የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ስራ እንደሚሰራም ሀላፊው አስገንዝበዋል።

የብልፅግና ፓርቲ አዲስ አበባ ቅ/ጽ/ቤት ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ማስባበሪያ ዘርፍ ምክትል ሀላፊ አቶ ወንዱ አሰፋ በበኩላቸው ከውስጥ ወደ ውጭ እየሰፋ የሚሄድ የህዝብ ግንኙነት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልፀው ዘርፉ ለአገር ግንባታው የድርሻውን ለማበርከት ባለፈው ሩብ ዓመት አበረታች እንቅስቃሴዎችን ማድረጉን አብራርተዋል።

ሚዲያን ለከተማችንና ለአገራችን ሰላምና ብልፅግና በማዋል የህዝብን አብሮነት እና የአገርን አንድነት ለማጠናከር በሩብ ዓመቱ የተጀማመሩ ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልፀዋል።

በውይይቱ መጨረሻ በ2015 ዓ/ም የላቀ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ክ/ከተሞች የእውቅና እና የምስጋና ፕሮግራም ተከናውኗል።

የቅርብ ዜና


Loading...